Category Archives: Books

አንድ የፋኖስ መብራት

አንድ የፋኖስ መብራት በግብሩ የኮራ፤
እንዲህ ሲል ተጣላ ከብርጭቆ ጋራ፡፡
‹‹እኔ ነኝ መብራቱ ብርሃን የምሰጥ፤
ጨለማን አጥፍቼ የምገላልጥ፡፡
አንተ ግን ከፊቴ እንዲህ ተደንቅረህ፤
ዙሪያዬን ከበኸኝ እንዲያው ተገትረህ፡፡
አልገባኝም ከቶ የምትሰራው ስራ፤
ብርሃኔ ሩቅ ደርሶ ደምቆ እንዳያበራ፤
አንተን ፈጠረብኝ መንገድ የምትዘጋ፡፡
እንቅፋት እየሆንክ ስራዬን አታጥፋ ፤
ገለል በል ከፊቴ ብርሃኔ ይስፋፋ፡፡››
‹‹አገልግሎቴማ ከሆነብኝ ጥፋት፤
እውነት ላንተ ከሆንኩህ እንቅፋት፡፡
ልሂድልህ›› ብሎ ሲለቅለት ቦታ፤
ከጎን የነፈሰ የንፋስ ሽውታ፣
መጣና መብራቱን አጠፋው ባንዳፍታ፡፡
አጭር እየሆነ ተመልካችነቱ፣
መለየት አቅቶት ጥቅሙን ከጉዳቱ፣
እወቁኝ እወቁኝ እያለ ሲነሳ
ሰውም እንደዚሁ ያመጣል አበሳ፡፡

(ዶ/ር ከበደ ሚካኤል)

ሽልንጌን

ሽልንጌን! ሽልንጌን!

ብርቱኳኗንና መንደሪኗን ይዛ ወደ መንገደኞቹ ባቡር ተጠግታለች:: በጀርባዋ ያዘለችው ሕፃንም “እምቢየው ወደ ቤት እንሂድ፤ እሪ…” እያለ ይነጫነጭባታል::
የእንጀራ ነገር ነውና ይህን የያዘችውን ፍራፍሬ ሳትሸጥ የሕፃን ልጇን ጉሮሮ መዝጋት አትችልም፤ በአንድ እጇ በጀርባዋ ያዘለችውን ሕፃን እያባበለች በሌላ እጇ
ደግሞ የተሸከመችውን የፍራፍሬ ሰሀን ወደ መንገደኞቹ እያስጠጋች ባቡሩ ከመንቀሳቀሱ በፊት ለመሸጥ በየመስኮቱ ትንጠራራለች:: ይህን ጊዜ ነበር አንዱ
መንገደኛ እንደ ዘበት በመስኮቱ በኩል እጁን ወደያዘችው ፍራፍሬ ሰዶ አንዱን ያነሳው:: “ሽልንግ” ነው ብላው ሂሳቧን እስኪሰጣት ድረስ በጉጉት
ትጠባበቃለች:: እሱም ሽልንጉን ያስቀመጠበትን ኪሱን መፈተሽ ጀምሯል:: በቀኙ.. በግራው… በፊቱና በኋላዉ ኪሶቹን ይዳብሳል:: የባቡሩ ሞተር መሞቅ ጀምሯል::
መንገደኞች ቦታ ቦታቸውን ይዘው የጉዞውን መጀመር ይጠባበቃሉ:: የባቡሩ ጭስ እየተግተለተለ መውጣት ጀምሯል:: ፋርጎዎቹ መነቃነቅ ጀምረዋል:: ያች
ምስኪን ግን ልቧ ተሸብሯል:: “ኧረ ሽልንጌን” ማለቱን ተያያዘችው:: ደጋግማ ተጣራች:: ፋርጎው ተንቀሳቀሰ ሰውዬው መንደሪኑን በእጁ እንደያዘ
በሌላኛው እጁ ደግሞ ሽልንጉን ከተቀበረበት ፈልጎ ማውጣቱ ላይ እንዳተኮረ ነው:: አሁን ባቡሩ እየሄደ ነው:: እሷም
“ሽልንጌን!…ሽልንጌን!…ሽልንጌን!” እያለች ባቡሩ እየተከተለችው ነው:: ባቡሩ ሄዷል:: የሷም ድምፅ በሩቁ ያስተጋባል::
በቀጭን ሰላላ ድምፅ ‹‹ሽልንጌን ሽልንጌን ››እያለች ትጮኸ ጀመረ፡፡ ከባቡሩ ሞተር ግምግምታ፤ ከተሳፋሪዎችና ከሻጮቹ ጫጫታ በላይ ለማሰማት የሚጣጣር ኡኡታ ነበረ፡፡ ‹‹ሽልንጌን ሽልንጌን›› …..ሽ….ል….ን….ጌ……ን…..

የቀድሞው የስምንተኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መጽሐፍ